10 መሰረታዊ የውል አተረጓጎም ደንቦች

***

በዳንኤል ፍቃዱ ( ጠበቃ እና የህግ አማካሪ)

***

ውል ቅኔ መሆን የለበትም። በተቻለ መጠን ለሁሉም ተዋዋይ  ወገን እንዲሁም ለሶስተኛ ወገኖች ጭምር ግልፅ በሆነ መንገድ መደረግ አለበት ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በተለያየ መንገድ የሚደረጉ ውሎች ግልፅነት የጎደላቸው ይሆኑና የግጭት ና ያለሙግባባት  መንስኤ ሆነው ለትርጉም አስማሚ ወይም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። ይህ ሲሆን ፍርድ ቤቶች ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ መሰረታዊ የሆኑ የውል አተረጓጎም ደንቦች አሉ። እነሱን እጠር አርገን ከተያያዥ የሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉሞች ጋር  እንመልከት:

የውል አተረጓጎም መሰረታዊ ደንቦች

1. ውሉ ግልፅ ከሆነ ምንም አይነት ትርጉም አያስፈልግም። ( If the contract is clear no need of interpretation ) /፩/

2.  የውሉ ትርጉም ውጤት መገኘት ያለበት ከራሱ ከውሉ እንጂ ፣ ውሉ ወይም ግዴታው ከትርጉሙ ሂደት መመንጨት የለበትም። / The interpretation of the contract must come from the contract not the contract from the interpretation./  በሌላ አማርኛ ፍርድ ቤት ውልን በመተርጎም ስም ያልነበረ ውል ወይም ግዴታ ሊፈጥርና ሊሰራ አይችልም።

3. የቅን ልቦና አተረጓጎን ደንብ (1732)  :- ማንም ሰው የራሱን መብት በአግባቡ ከመጠቀም አልፎ በሌላው ተዋዋይ ላይ አላስፈላጊ ጉዳት የማድረስ ፍላጎት የለውም የሚል አወንታዊ  መነሻ ሃሳብ ( positive premise) አለ። ከዚህ ተቃራኒ የሄነ ሃስብ ይዞ ከቅን ልቦና በተቃራኒ ጉዳት ለማድረስ ያለው ተዋዋይ ወገን ካለ ህግ በመርህ ደረጃ ጥበቃ ያደርግለታል። /፪/

4. በተገቢው መንገድ ያልተብራሩ ሃሳቦችን አተረጓጎም በተመለከተ ለልማዳዊ አሰራሮች እና አፈፃፀሞች በቂ ትኩረት ሊቸረው ይገባል። ውል ከአካባቢው አሰራርና ተቀባይነት ካላቸው ልምዶች አንፃር እየተገናዘበ መተርጎም ይኖርበታል።

5.  አሻሚ የሆኑ ቃላት እና ሃረጎችአተረጓጎም፣

" A plain contract means what it says " 

ግልፅ የሆነ ውል የውሉ ቃላት በቀጥታ የሚያስተላልፈው ትርጉም ብቻ ነው

በተቃራኒው የውሉ  ሃሳብ ግልፅ ካልሆነና አሻሚ ከሆነ ግን   የተዋዋዮች ሃሳብ ምን እንደሆነ ለማወቅ ተገቢውን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም ማለት ትርጉም በመስጠት ሂደት ውሉን እንዲተረጉም የቀረበለት አካል ትርጉሙን የሚፈልገው በውሉ ውስጥ ከሚገኙ ቃላት ላይ ብቻ አይደለም ። ውሉ ለድርድር ( ለስምምነት ) በቀረበበት ጊዜ ( Offer and Acceptance )  ፣ እንዲሁም የውሉ ድርድር በሚካሄድበት ጊዜ ፣ ድርድሩ በቀረበበት እና ተቀባይነት ባገኘበት ጊዜ ፣ ከዚያም በፊት የተከናወኑ ቀዳሚ ግንኙነቶች በተደረጉበት ጊዜ የተደረጉ እና የተከናወኑ ጉዳዮች ሁሉ ተገናዝበው ትርጉም ሊሰጣቸው ይገባል።

አሻሚ የሆነው ቃል አጠቃላይ አነጋገር ከሆነ በትርጉም የሚወሰደው የቃሉ የተለመደ ትርጉም ነው።

በቅጡ ተለይቶ ያልታወቀ የውል ፍሬ ነገር ( Object ) ካለ ሁሉንም የውሉን ቃላት አረፍተ ነገሮች አንዱን ከአንዱ በማገናዘብ የመጨረሻ ትርጉም ላይ መድረስ ይቻላል።/፫/

6. ከውሉ ባህርይ ጋር የሚቀራረበው ትርጉም ከማይቀራረበው ይመረጣል።

7.  ውሉን ዋጋ ከሚያሳጣው ትርጉም ይልቅ ውጤታማ የሚያደርገው ይመረጣል።/፭/ 

8.  የውሉን ባለመብት ከሚጠቅመው ባለዕዳውን የሚደግፈው ይመረጣል።/፬/

9. ውሉን ካዘጋጀው ወገን ይልቅ ውሉን ላላዘጋጀው የሚጠቅመው ትርጉም ይመረጣል።

10. ያለዋጋ በተደረገ ውል  ( Gratuitous contract) በውሉ መብት ካገኘው ሰው ይልቅ ውሉ ግዴታ ለሚጥልበት ሰው የሚጠቅመው ትርጉም ይመረጣል።/፮/ /፯/


ተዛማጅ የሰበር ውሳኔዎች 

/፩/  ሠ/መ/ቁ 15662 ( ቅፅ 4) - ውሉ ግልፅ በሆነ ጊዜ ግልፅ ሆኖ ካለው ሃሳብ በመራቅ የተዋዋዮቹ ፍቃድ ምን እንደነበር ዳኞች ለመተርጎም አይችሉም።

/፪/  ሠ/መ/ቁ 25165 (ቅ.7) የቅን ልቦና መከራከሪያን ወደጎን በመተው ውልን ተርጉሞ አንድን ውል ማፍረስ ትክክል አይደለም።

/፫/  ሠ/መ/ቁ 38544 (ቅፅ 10) - ተዋዋዮች ውላቸውን ከመዋዋላቸው አስቀድመው ወይም ከተዋዋሉ በኋላ የነበሩትን ሁኔታዎች ፣ የፈፀሙትን ተግባራት በማመዛዘንና ሃሳባቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ መሞከር ፣ የውሎችን ቃላቶች አንዱን ከአንዱ ጋር እያዛመዱ መመልከት ለውሉ ጉዳይ አግባብ ያለው ትርጉም ለመስጠት ተገቢ ነውና

/፬/  ሠ/መ/ቁ 41893 (ቅፅ 10) - የስጦታ ውል ሊተረጎም የሚገባው በውሉ ውስጥ የሚገኘውን አንድ ሃረግ ነጥሎ በማውጣት ሳይሆን የውሉን አጠቃላይ ይዘት በመመልከት ነው። 


/፭/  ሠ/መ/ቁ 27869 (ቅፅ 5 ) - የቤቱ መለያዎች እና ቦታ ሳይጠቀስ አንድ ቤት ለማክበር በአይነት መዋጮ ቢሄንና ሰውየው ያለው አንድ ቤት ብቻ እንጂ ሌላ ቤት የሌለው ከሆነ በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1723 መሰረት ሲተረጎም በውሉ ላይ የተገለፀው  እያዋጣው ያለውን አንድ ቤት እንደሆነ መተርጎም አለበት። ስመ ንብረቱ በማህበሩ ባይመዘገብም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 2878 መሰረት ለ3ተኛ ወገን መቃወሚያ እንዳይሆን ይከለክላል እንጂ መዋጮውን ውጤት አያሳጣውም።

/፮/  ሠ/መ/ቁ 103910 ( ቅፅ 10 ) - በውሉ ውስጥ አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም የውሉ ድንጋጌ መተርጎም ያለበት በውሉ አስገዳጅ ( ባለመብት ) የሆለው ወገን በሚጠቅም ሁኔታ ሳይሆን በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1738 መርህ  መሰረት በውል ተገዳጅ ለሆነው ሰው ምቹ በሚሆንበት አኳኋን ነውና

/፯/  ሠ/መ/ቁ 107990 (ቅ.17) - በግልፅ የሰፈረ የውል ቃል ባይኖርም ስጦታ ሰጪው በድህነት ላይ ወድቆ እያለ ስጦታ ተቀባይ የምክር ግዴታ ያለበት ሲሆን ስጦታ ተቀባይ ከስጦታ ሰጪ የተቀበለውን የእርሻ መሬት እየተጠቀመ በውለታ ቢስነት ስጦታ ሰጪውን የሚጎዳ ተግባር ፈፅሞ ከተገኘ ስጦታ ሰጪው ውሉ እንዲፈርስለት የመጠየቅ መብት አለው።

Comments

Popular posts from this blog

የአጣሪ ዳኝነት ሚና በአስተዳደር ህግ

በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የሚቀርብ ክስን ማየት ስልጣን ያለው ማነው? በዳንኤል ፍቃዱ ( ጠበቃ እና የህግ አማካሪ)

ተወካይ የወካዩን እማይንቀሳቀስ ንብረት አስይዞ መበደር ስልጣን .... የሠ.መ.ቁ. 17320 / ቅፅ 5 / ላይ እና በመዝገቡ ላይ በኢትዮጵያ ጠበቆች የህግ መፅሄት መግዌ 5 ቁ.2 ላይ በተሰጠው ትችት ላይ የተሰጠ የትችት ትችት .....