ተጠሪ

 ተጠሪ

*

        ዳንኤል ፍቃዱ / የህግ አማካሪና ጠበቃ/

*

አንድ ተቋም ለአንድ ሌላ ተቋም ወይም ግለሰብ ተጠሪ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ምን መብት ምን ግዴታስ በተጠሪው ላይ ይፈጥራል? በጠሪው ( ይጠራልህ በተባለው)ግለሰብ ወይም ተቋም ላይስ? 


ከህገ መንግስቱ አንስቶ መመሪያ ድረስ ያሉ ህጎች ላይ ይህች ቀላል እምትመስል ቃል በየቦታው ተዱላ እንመለከታታለን ። በእንግሊዝኛው በተለዋዋጭ Accountable ወይም Responsible በሚል ተገልፃ እናገናታለን።


 እውቁ የህግ መዝገበ ቃላት Blacks law Dictionaryንም ስንመለከት ቃላቱ በተለዋዋጭ / interchangeably/ አገልግሎት ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ሲያጠይቅ:


Accountable = Responsible በሚል ይተረጉመዋል።

ስለዚህ ሃላፊነት፣ ተጠያቂነት፣ መልስ ሰጪነት ፣ ወዘተ ተብሎ ሊተረጎም ይችል ይሆናል።


ለምሳሌ ያህል ፩/  የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 49 (3) ላይ " የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት ይሆናል። " ይላል። ምን ማለት ይሆን ?ሰበር በሠ/መ/ቁጥር 34665 ቅፅ 10 ላይ


 " የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ስራ የመከታተልና በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣን ያለው እንደመሆኑ መጠን የስራና ከተማ ልማት ሚኒስትር ቤቶችን የሚመለከት ጉዳይ ለአዲስ አበባ ስራና ከተማ ልማት ቢሮ እንዲያስተላልፍ በተሰጠው ትዕዛዝ ( ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤ ባስተላለፉት ) መሰረት ስራውና ሰራተኞችን ለቢሮው አስተላልፏል ። " 

ይለናል ይህ ማለት እንግዲህ  የከተማ መስተዳድሩ በሚያወጣቸው ህጎች እና በሚወስናቸው ውሳኔዎች ሁሉ የፌደራሉን ይሁንታ ማግኘት አለበት ማለት ነው? ፌደራሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣው ህግ እና የወሰነው ውሳኔ ካልተስማማው ሊሽረው ፣ ሊያስተካክለው ወይም ሊለውጠው ይችላል ማለት ነው? ከላይ በሰበር ውሳኔው እንዳየነው በደብዳቤ ሲፈልግ ስልጣን ሊጨምርለት ሲፈልግ ሊቀንስ ይችላል ማለት ነው? 


የግንቦት 1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በተፈጠረው ቀውስ ሰበብ ወደ  ፌዴራል መንግሥት የተዘዋወረውን ( ዛሬ መንገድ ዘግቶ ማሊያውን ሲያስመርቅ የዋለው ( በሌላ ቅንፍ ( ከንቲባዋ ምን እገባኝ ብለው ነው ለማይጠራቸው አካል  ላይ ታች ሲሉ የዋሉት??))) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ጉዳይም ስንታዘብ የቃሉ ትርጉም ምን ያህል ለትርጓሜ አዳጋች መሆኑን ማሳያ ነጥብ ነው። ተጠሪነት ማለት ሲፈልጉ መውሰድ ሲያሻ መመለስ ማለት ነው ወይ? 



ምሳሌ ፪/ አሁንም  የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ76(2) ላይ " የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። "   ብሎ ይደነግጋል የኢፌድሪ የፌደራል አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀፅ 11 (1) ደሞ 


" እያንዳንዱ ሚኒስትር ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሆናል። " ይለናል።  ይህስ ትርጉሙ ምን ይሆን ? ሰበር ሰሚው በሠ/መ/ቁ. 16195 (ቅ 4 ) ላይ እንደ ሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም 


"ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የፈፀሙትን ስህተት ማረምና ማስተካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ነው " 


ምን ማለት ይሆን? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ሁሉ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ( በሙያው ልዩ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች የተቋቋመ እና የሚመራ ነው ተብሎ መገመት የሚችል) ይህ ውሳኔህ ልክ አይደለም፣ ይሄን ህግህን  ደግሞ እሻሽል ፣ እቺን ጨምር ፣ ኢሄን ቀንስ የሚል ከሆነ ጣልቃ ገብነት አይሆንም? በምን ህግስ ነው ይህ ስልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው? ህገመንግስታዊነቱስ እንዴት ይታይ? ተጠሪ ይሆናል ማለት እንደዚህ ነው? 


ባጠቃላይ ብዙ ህጎችን ጠቅሶ የተጠሪነትን ትርጉም መመርመር እና መተቸት ይቻላል። ከቃሉ ተዘውታሪነትና ከላይ በትንሹም ቢሆን ለማሳየት እንደተሞከረው ሊፈጥረው ከሚችሉው የወጥነት ችግር አንፃር ህግ አውቀው ና አስፈፃሚው በሚያወጧቸው የተለያዩ ህጎች ቃሉን ሲጠቀሙ ድንበር እና ገደብ ቢያበጁለት መልካም ነው። ህግ ተርጓሚውም ህጉን ሲተረጉም የህጉ አላማ ምንድነው? የእውነት ይሄ ስልጣን በተጠሪነት ስም ለአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ሊሰጠው የሚገባ ነው ወይ ? የሚለውን ከግምት ውስጥ ሊከቱት ይገባል።

Comments

Popular posts from this blog

የአጣሪ ዳኝነት ሚና በአስተዳደር ህግ

በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የሚቀርብ ክስን ማየት ስልጣን ያለው ማነው? በዳንኤል ፍቃዱ ( ጠበቃ እና የህግ አማካሪ)

ተወካይ የወካዩን እማይንቀሳቀስ ንብረት አስይዞ መበደር ስልጣን .... የሠ.መ.ቁ. 17320 / ቅፅ 5 / ላይ እና በመዝገቡ ላይ በኢትዮጵያ ጠበቆች የህግ መፅሄት መግዌ 5 ቁ.2 ላይ በተሰጠው ትችት ላይ የተሰጠ የትችት ትችት .....